| 21.03.2010 | 15:00 UTC
ካይሮ፣ ዓለም- አቀፍ የመዋጮ ስብሰባ ለዳርፉር መልሶ ግንባታ፣
በ 7 ዓመታት ጦርነት ለተዳቀቀው የሱዳን ምዕራባዊ ክፍለ-ሀገር ፣ ዳርፉር፣ መልሶ-ግንባታ ፣ 2 ቢሊዮን ዶላር ለማዋጣት አቅድ የተያዘለት ጉባዔ በካይሮ ግብፅ ተካሄደ።
የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ መንግሥታት ማኅበር ያዘጋጀውና ግብፅና ቱርክ በኅብረት ያስተናገዱት ጉባዔ የተካሄደው፣ በሱዳን አጠቃላይ ምክር ቤታዊ ምርጫ ከመደረጉ 3 ሳምንት ቀደም ብሎ ነው። ምርጫው፣ ነጻና ፍትኀዊ የሚሆንበት ምልክት ከወዲሁ ሊታይ አለመቻሉን ታዛቢዎች በመግለጽ ከማስጠንቀቅ አልቦዘኑም። 57 የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ መንግሥታትና 25 ያይደሉ፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪቃ ኅብረት፣ የዐረብ መንግሥታት ማኅበር እንዲሁም 50 ያህል ሌሎች ዓለም አቀፍና የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች በጉባዔው እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል። ለዳርፉር የመልሶ ግንባታ መዋጮ ነክ ጉባዔ የተከፈተው፣ የካርቱም መንግሥትና ዋናው የዳርፉር አማጺ ኃይል (JEM) ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተኩስ ለማቆምና ዘላቂ የሰላም ውል ለመፈራረም ከተስማሙ ወዲህ ነው። ይሁን እንጂ ዘላቂ የሰላም ውል ለመፈረም ባለፈው ሳምንት ተይዞ የነበርው ቀነ-ቀጠሮ እንከን እንዳላጣው ተገልጿል።










